04/08/2026
የአለም ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እየተነጋገሩ ነው
በአንድ ጀምበር 805 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የተመዘገበው ታሪካዊ ስኬት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች አድርጓታል። ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በነቂስ በመውጣት ያሳዩት የማይበገር የአንድነትና የባለቤትነት ስሜት፣ ሀገራችን በራሷ አቅም የተፈጥሮ ሀብቷን የመንከባከብና የደን ሽፋኗን የማሳደግ ጽኑ አቋም እንዳላት ለዓለም ያስመሰከረ አበይት ኩራት ነው።
ዓለም በከባድ የበረሃማነትና የአየር ንብረት መዛባት ስጋት ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ይህ የኢትዮጵያ ግዙፍ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ለአፍሪካም ሆነ ለተቀረው ዓለም አርአያ የሚሆን ተግባራዊ መፍትሔ አሳይቷል። በሀገር ውስጥ ከተከናወነው በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር መርሃ ግብሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማካሄዳቸው፣ ሀገራችን ለምድር ጤናማነትና ለዘላቂ ልማት ያላትን መሪነትና ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው።