21/01/2026
ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቡና በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ።
ግምታዊ ዋጋው 8,744,000 ብር የሆነ ቡና በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የአዋሽ ከ/መስተዳድር ፖሊስ ፅ/ቤት አስታወቀ።
ፅ/ቤታቸው በማህበራዊ ሚዲያ ባጋራው መሰረት የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ኮማንደር ጦይብ አሊ ሀሰን በስልክ ባደረግንላቸው ቃለ መጠይቅ ለአፋር ቲቪ እንደገለጹት ህገ-ወጥ ቡናው የተያዘው ትላንት ከምሽቱ ሰባት ሰዓት ላይ ነው ብለዋል።
የተያዘው ቡና መጠኑ 136 ኩንታል ሲሆን ህገ-ወጦች ቡናውን ከመቱ ከተማ ጭነው አዲስ አበባ እንዲራገፍ የታቀደ ነበር ።
ቢሆንም በህገ-ወጥ መንገድ የተሳሳተ ሰነድ በማሰራት ጭነቱን ከታለመለት አላማ ውጭ ወደ ደሴ ከተማ በማዘዋወር ላይ ሳሉ አዋሽ ከተማ ሲደርስ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ የአዋሽ ከተማ ፓሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለው ኮማንደሩ ገልፀውልናል።
የአዋሽ ከተማ ፖሊሶች ከህብረተሰቡ በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመሆን ተሽከርካሪውን በከተማዋ መግቢያ ላይ በሚገኝ የቁጥጥር ኬላ በመዝጋትና ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ህገ-ወጥ ጭነቱን መያዛቸውን አመልክተዋል።
ጭነቱን ሲያዋውር የነበረው ተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A06451 አአ የሆነ አይሱዙ FSR መኪና ሲሆን ጭነቱ 136 ኩንታል ቡና ግምታዊ ዋጋው 8ሚሊዮን 744ሺ ብር እንደሆነም ከፖሊስ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ህገ-ወጥ ቡናውን ለመያዝ በተካሄደ ዘመቻ ለተሳተፉ አካላት እና ህብረተሰቡ ላደረሳቸው ጥቆማ በጽህፈት ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል
, , , , ,